፠ የእናኑ መልዕክት ለሽሮሜዳ ዜጋዎች

An excerpt from መረቅ (Mereq) by Adam Reta

Issue 1 - April 2026

‘እናኑ’ ወይም ‘እናና’ የምንላት አያቴ የምትኖረው መስፍን ሃረር መንገድ ነው። በትክክል የደም ግንኙነት የለንም፣ ግን ከሴት አያቴ ከሰብለ ጋር እንደ እህትማማቾች ነበሩ። የምትናገረው ነገር ሁሉ እንዲደመጥ፣ የሚሰ’ራ ከሆነ እንዲፈጸም የምትፈልግ ቀልድ የማታውቅ ሴትዮ ናት። ብዙ ጊዜ ወደዚህ ወደ ሽሮሜዳ ነይና ኑሪ እያልናት ‘ያረጀሁበትን ቤቴን አለቅም’ ብላን ሁልጊዜም እዛ ናት። ቤቷ ለመድረስ በታክሲ ግማሽ ሰአት ይወስድብኛል። ሁልጊዜ እሷ ጋ ስሄድ ከሽሮሜዳው ዋህድ ሸንኮራ እገዛላታለሁ። ጥሩ ሸንኮራ የሚያውቀው ዋህድ ነው፤ ከሌላ እንዳትገዛብኝ ትላለች። አንድ ሁለቴ ሸውጄአት እንደሸወድኳት ገብቷታል።

ሳንቲሜን ሱሪ ኪሴ ከትቼ ከግቢ ወጣሁ። ወደ ላይ አየሁ። እህል ፈሶበት አስፋልቱ በእርግቦች ተሸፍኗል። መኪና ሲጠጋቸው ይነሱና ካለፈ በኋላ ወደ ለቀማቸው ይመለሳሉ። ከእነሱ ዝቅ ብሎ ዋህድ መንገድ ዳር እንጀራና ቂጣ ከምትነግደው ማልደያ ከተባለች ሴትዮ ጋር ቆሞ ያወራል። ስጠራው ቢሰማኝም ወሬውን ማቋረጥ አልቻለም፣ ወይም ሴትዮዋ ልትለቀው አልፈለገችም። ቢሰማኝም ባይሰማኝም መንገድ ተሻግሬ የስሙኒ ሸንኮራ እንዲሰጠኝ በጩኸት ጠየቅሁት። ከሴትየዋ ጋ እያወራ ሴንጢውን ከደረት ኪሱ አውጥቶ ሸንኮራ መቁረጥ ጀመረ።

“ስራ አላስፈታህ፣ ደህና ዋል!”

“ደህና ዋይ ማልዴ፣ ብቅ እላለሁ ወደ ማታ። ጠብቀኝ በይው”

“እለዋለሁ”

መንገድ ሳቋርጥ ከሴትዮዋ ጋር ተላለፍን። የተቆላ ስንዴ ጠረን ወይም የቆሎ ጠረን ትሸታለች። ስህተት እንዳጋጠመኝ ሁሉ ዞር ብዬ አየሁዋት። እኔን እንዳለፈች ከጀርባዬ በኩል ወደ አለው የኮረኮንች መንገድ ቶሎ ቶሎ እየተራመደች ገባች። ከሆነ አባራሪ የምትሸሽ ትመስላለች።

“አላዛር እናኑ ጋ ነህ መሰለኝ?” አለ ገና ሳልጠጋው ዋህድ

“አዎ”

“እሳቸው ከነአንጓው ነው የሚወዱት አይደለም? አንጓውን ለሁለት መሰንጠቅ ከባድ እኮ ነው፣ እንዴት አንድ መለልታ ሁለት አንጓ ይኖረዋል?”

“አድርግልኝ ያለችውን አድርግላት”

“የምትሞት አሮጊት አትርገምህን ተረት ፈርተህ ነው” አለ እየሳቀ

“በተረት አትዶክከኝ ባክህ”

“ጨዋታ ነው፤ ውሰድ ይሄውልህ፣ ላጥ ነው የማደርጋት እኔ ዋህድ። በምንህ ትይዘዋለህ?”

“ከተማም ሱቅ ላስቲክ እወስዳለሁ”

“ተማም የላስቲክ ፋብሪካ አለው? እዛ ድረስ በምን ትወስደዋለህ?”

“ምን አገባህ?”

ዋህድ የተሳሰሩ ሶስት የሸንኮራ ዘንጎች አቀበለኝና ሳንቲሙን እንድሰጠው እጁን ዘረጋ። ስሙኒውን ሰጠሁት። ሴንጢና ሸንኮራ እያጋጨ እንጉርጉሮውን ጀመረ....

ለእናኑ የገዛሁላት ሁለት ዘንጎች እያንዳንዳቸው ሁለት መለልታና ሶስት አንጓ አላቸው። ዋህድ ብዙ ጊዜ አንጓውን በትክክል ከመሃል መቁረጥ ስላለበት ያማርራል። ማንም ሰው ከእናኑ በስተቀር እንዲህ እንዲቆረጥለት አይጠይቅም።

ሸንኮራዬን ይዤ ልክ ዘጠኝ ሰአት ላይ መስፍን ሐረር መንገድ ደረስኩ። የእናናን የግቢ በር ሳንኳኳ እንዳላበኝ አወቅሁ። ጃኬቴን አወለቅሁና በትከሻዬ ያዝኩት። ገና እንደተከፈተልኝ እናናን ከቤቷ በረንዳ ታች ደረጃ ላይ ተቀምጣ አየኋዋት።

“የእኔ ጌታ መጣህ! የእኔ ደራሼ! የእኔ መኳንንት!”

ላስቲኬን አንጠልጥዬ እንደተጠጋሁዋት ፊቴን በሁለት እጆቿ ይዛ አፌን፣ ግንባሬን ፊቴን ሳመችኝ።

“ስትጣፍጥ፣ አቤት ስትጣፍጥ” አለች አፏን እየዳበሰች።

ቀዝቃዛ ነው ፊቷ። ምናልባት ቆዳዋ የግቢው ዛፎች ሳያቋርጡ ከሚፈጥሩላት ጥላ የተቀበለው ይሆናል። ብዙ ጊዜ እዚህ ስትቀመጥ ወይ ጥፍሯን ትቆርጣለች ወይ ሸንኮራ ትበላለች። ሸንኮራዋን በልታ ጨርሳ ጣቶቿን ተራ በተራ ታያለች። ጥፍሯ ያደገ ከሆነ እሱን ትከረክማለች። ከሶስቱ ደረጃዎች አንዱ ላይ ሁልጊዜ ጥፍር መቁረጫ አይጠፋም። የደረጃዎች መጋጠሚያ ላይ መአት የእናና የጥፍር ቁርጥራጮች ነፋስ ዝናብ እየገፋና እየሰበሰባቸው የደቃቃ አጥንት ስብርባሪዎች መስለው ይቀመጣሉ። የሚጠርጋቸው የለም። ጣቶቿን አየሁ። ንፁህ ሆነው ተከርክመዋል። ጥፍር ማቁረጫ፣ ዱባ ወጥና ሸንኮራዋን ካገኘች እናና አትጨነቅም። የቁሳቁስ ፍቅሯ በነዚህ ብቻ መወሰኑ አንዳንዴ ይገርመኛል።

“በል አምጣ ሸንኮራዬን”

ግቢው በረዣዥም ያረጁ ዛፎች የተከለለ ነው። ባማይጨው ጦርነት ጊዜ የአንድ ጣሊያን መኮንን መኖሪያ የነበረ ነው። ከፊት ለፊቱ ያለው ቦታ በአበቦችና በትላልቅ የኮባ ተክሎች ግርማ ተሞልቷል። ላስቲኩን ስሰጣት ተቀበለችኝ እና ከቂጡ ይዛ ዘቀዘቀችው። ሸንኮራዎቹ እየተንከባለሉ ወጡ። እተጋደሙበት ለአፍታ ተራ በተራ ስታያቸው ቆየችና፣ አንዱን አነሳች። አገላብጣ አይታ በነጠላዋ ጠራርጋ ትላልቅ ጥርሶቿን አንጓው ላይ ተክላ መቆፈር ጀመረች።

“እኔ እናትህ ቀላል አልምሰልህ....” በግራ እጇ ጎና እንድቀመጥ ደረጃውን ተመተመች።

“ና እዚህ....ፊቴ አትቁም”

ሸንኮራውን በደቂቃ ላጠችና ማላመጥ ጀመረች። ወለላው ከአፏ ሲወጣ ለምቦጯን በመዳፏና በነጠላዋ ትጠርጋለች። ዞር ብላ አየችኝና: “ገፅህ እኮ እያትህን ሰብልዬን ቁጭ” አለች።

ሁልጊዜ የምትለኝ፣ የማይሰለቻት ግን እኔን ያማረረኝ መረጃ ነው።

“ልጅ ብዙ ጊዜ እናቱን ወይም አባቱን ነው የሚመስለው። አያት ጋ ምን አስኬደ? እያትህ ሰብለ እርግብግብ ነበረች። ለትንሹ ነገር ‘የዲማው ያለህ’፣ ‘የዲማው ድረስ’፣ ምን ፈረሰኛ ቢሆን ከብቸና እዚህ... ይቅር በለኝ....ሁሉ ነገር ያሳስባታል እምጠ አይ ሸንኮራ እቴ። እንደው መመሳሰላችሁ የእግዜር ስራ ይመስለኛል። እናትህን ሮዛን ሞጆ ነው የወለደቻት፤ ያን ጊዜ አራስ ሆና ያየሁት አይኗን አሁን እዚህ ቆመህ አየሁት። በልቤ አይ መመሳሰል አልኩ። እሷን እንዳልረሳት ነው እግዜር በጥበቡ አንተን የሰራው። የምረሳት መስሎታል፤ ቂሉን ይፈልግ። ታዲያ አያት ድረስ ይኬዳል? ሊያባባ ካልሆነ? ሁሉን ነገር ካስተዋሉት ያስገርማል። የኑሮ ትንሽ የለውም። እዛ የወደቀችው ደረቅ ሳር አስገራሚ ናት። ወፍ ለቅሞ ጎጆ ይሰራባታል። ይሄን ሳር አጭዶ ያመጣው ማጭዱ አስገራሚ ነው። ሰዎቹ ማጭድ ማሰባቸው። የሚያስገርመው ጉዳይ እልፍ ነው። ሳሩን አጭዶ ያመጣልኝ ሰውዬ ‘ዘገየ’ ይባላል ጨዋታ ያውቃል። እሱ ሲያወራኝ የሚገርም ነው ታሪኩ። ‘ለምን?’ ብትል እንደው ወንድ ሆነ እንጂ ታሪኩ ተእኔ አንድ ነው። የእኔ ታሪክ ምንም ብለፋ ምንም ብቀባጥር የእኔ ብቻ አይሆን። ለካ የእሱ የእኔን ይመስላል ብለህ መታዘብ አለ። ያንተ የአንተ ተሆነ፣ የእናትህ የእናትህ ተሆነ የሰብለ የሰብለ ተሆነ እንዴት እዝህ ደረስን። እሱ እኮ ነው። ጠዋት እዚህ ፀሐይ ስሞቅ የቆረጥኩት የአውራጣቴ ጥፍር ለስንት ጉንዳን እራት ይሆናል? ባላርስም አበላሁ ማለት ነው.... ሂሂሂ”

‘ግድ የለኝም’ እንዳልላት ነጭናጫነቷን መቀስቀስ አልፈለኩም

“ትሰማኛለህ?” አለች

መሬት መሬት እያየሁ ራሴን በአወንታ ነቀነቅሁ። የሸንኮራው መረቅ በነካቸው ጣቶቿ ፀጉሬን ደባበሰችና

“አይ ፀጉር እቴ .... እንዳልኩህ አዝዬ.... ሰሚ ታገኘ የማንም ታሪክ ይገርማል። እንደው እየመረጥን እንጂ.... ሰብለ የሚነገር ታሪክ ነው ያላት። እግዜር በመጣፉ ጫር ጫር ያደርጋል እኛ እንኖራለን። ዝም ብለን መኖር ....የሰብለ ታሪኳን ተረት በለው። ምን ሌላ ስም አለው? እሷ የፊታውራሪ ልጅ ነበረች።

“በእናትህ በኩል ቅድመ አያትህ ፊታውራሪ መሸሻ የሚባሉ አጥንተ ጥሩ የጎጃም ሰው ነበሩ። ሰብለ ዲማ ነው እንግዲህ የተወለደችው፣ ለአቅመ ሔዋን የደረሰችውም እዛ ነው.... አባቷ ባል ሲመርጡ መዳሪያ ጊዜዋ ተላለፋት.... እና ፊደል የሚያስቆጥራትን በዛብህ የሚባል ጎረምሳ ዲያቆን ወደደች። ያኔ እንደዛሬ ዘመን ማንም ከማንም አይጋባም። ዘር አለ ምን አለ....

“አባቷ ከሚንቁት ሰው የመዋደድዋ ወሬ ሲደርሳቸው ‘ይሄን ቅማላም ካልገደልኩ’ ሲሉ ይሰማና በዛብህ ነፍሱን ሊያድን ወደ ሸዋ ይሰደዳል። ቆየት ብሎ እሷ መሸሹን ስትሰማ ሳትውል ሳታድር.... አስረዋት አልነበር....ተእስር አምልጣ.... እግሩን ተከትላ ወደ ሸዋ። ብቻዋን.... ብዙ ብዙ ችግር አጋጠማት እሷ እንደምትለው። አንደዬው ‘አይኑን እዪው’ ሲላት በዛብህን ሽፍቶች ደብድበውት በጠና ታሞ ሊሞት ሲያጣጥር አንድ ባላገር ቤት ተኝቶ ትደርሳለች። እንደው ግጥጥሞሹ አይገርምም? ምን ይደርጋል እግዜር ያቀደውን?....አይታገሉት። ክንድዋ ላይ ደም መቶት ይሞታል። እንዲህ ስታወራኝ በጉንጭዋ ዕንባ እየወረደ ነው። ታሪኳን የሰማት ሁሉ ነው ‘ሚያለቅስ....ያቺ ልጅ አልመጣችም? መድሃኒቴን የት ነው ያስቀመጠችው? ጊዜው ተላለፈ እኮ። ሰዓት ስንት ሆነ? እምጣ

“....ስለ አያትህ ስለ ሰብለ ልቀጥልልህ። በዛብህ ሲሞትባት ‘ምን ቀረኝ ዲማ አልመለስም’ ብላ እሱን ደጀሰላም ቀብራ ነጋዴ ተከትላ አዲስአባ መጣች። አራዳው ጊዮርጊስ ነው ያገኘሁዋት እንደ ነዳይ አፈር ላይ ተኝታ። ከግንባሯ፣ ቀን ያጣላት እንደሆነች ማንም ይገባዋል። ቤቴ ወሰድኳት። እኔ ምን ነበረኝ ያኔ? ምንም። ሴት ነኝ የሁለታችንንም ሆድ መሙላት አልችል።

“አገሩን ስትለምድ ‘በይ ተነሽ አሁን’ አልኩና ብዙ ሳትቆይ ብቻ ከተማውን ለምዳለች ነጋዴ አደረግኳት። ቅጠላቅጠል፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ዱባና ቅል እሸጥ ነበር። አብረን መነገድ ጀመርን.... በተለይ የቅል ስራችን ጠነከረ። አሁን አርጅቼ አልሰራውም እንጂ ቅል መንቀስ፣ ማሳመር፣ ማሽመልመል እችል ነበር። በቅል ላይ በወስፌውም በካራውም ስዕልና ቅርጥ መስራት። ሐረጉን መከየን። መዳፌ በስለት ተቆራርጦ እንደው ወንፊት ይመስል ነበር....።

“ገበያችን ተአራዳው ጊዮርጊስ ስር ነበር የተነጠፈው፣ ትንሽ ፈቀቅ ብሎ። ሰብለ ለመሸከም ወገቧ አይችል በዛ ላይ ተእኔ የባሰች ባላገር። ግን ቆንጆ ነችና የማይወዳት አልነበረም። ቆንጆ ስልህ ይህቺ እዚህ ተግሮሰሪው ዝቅ ብሎ የሚኖሩ አለማየሁ ሀዲስ የሚባሉ ሰውዬ የሉም? ‘እንቆጳ’ የምትባል ልጅ አለቻቸው፤ እሷን አይተህ ማየት ነው። እንቆጳ ጠቆር ትላለች እንጂ። ገበያተኛው የሚያውቃት ‘የሸንኮራዋ ልጅ’ እያለ ነበር። እና ዱባችንን፣ ሸንኮራችንን መሸጥ ቀጠልን። ደምበኛችን በዛ። ዱባው ካልደረሰ ጎመኑን። ሽንኩርቱን እንላለን። ሁልጊዜም ግን ሸንኮራ አለን። ‘እዛ ቀይ ዳማዋ ጋ’ ‘ሸንኮሪት ጋ ሒዱ’ ይባላል። ተዓይን የማይደበቅ ምን እንደ ሆነ ታውቃለህ? ተራራና ቆንጆ....

ሸሽተሽ ተአራዳው ብትገቢ እሞጆ

ከዓይን አይሸሸግም ተራራራና ቆንጆ....

አለ ነገር አላለም ያገሬ አንጎራጉዋሪ። እኔ ለማጣራት ቀንና ሁለት ቀን የሚወስድብኝን እሷ ቁጭ አድርጋት ምጥት። አንዳንዴ መደቤን እየተውኩላት ቤት ቀርቼ ምግባችንን እሰራለሁ።

“እንዲህ እንዳለን አንድ ሰርኪን የተባለ አርመን አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሊሳለም ሲሄድ በዚያ በገበያው ሲያልፍ በየቀኑ ያያታል፣ እና ይወዳታል፡ ሲመጣ የያዘችውን ከዛም ከዛም ቀላቅሎ ይገዛትና ይሄዳል፣ አገሩ ሃብታም አርመን ነበር አሉ። የኛ ሰው ወሬውን ተየት እንደሚለቃቅመው። አንድ ቀን ሸቀጥዋን በጀርባዋ አዝላ ስትሄድ ይገጣጠማትና ይቆጣል.... ‘ምን ይላል?’ ‘ምን ይቀባጥራል?’ እያልኩ ገና ገበያ ዘርግተን እፎይ እንዳልን አንዲት አህያ አምጥቶ እንኪ አላት። በቃ አምጥቶ ይሄው። እኔ ‘ምን ማለቱ ነው? ጨዋ የጨዋ ልጅ ናት’

እላለሁ። አስተርጉዋሚ እሱን የመሰለ መጥቶ ‘ታርባኒ’ የሚባል ተዚህ ተአራዳ የማይጠፋ---ያኔ ቢያሳ የለም እሱስ --- ‘እሱ እኮ የሰጣት ስጦታ ነው... ክፉ አይደለም ያደረገው.... ቆንጆ ልጅ ናትና ገላዋ እንዳይጎዳ አስቦ ነው’ አለን። እሷ መሬት መሬት እያየች ‘አልቀበልም’። ‘ያገባሽ መሰለሽ? በይ የሰው ስጦታ እምቢ አይባልም’ ብለን እዛ የተሰበሰብን ሴቴ ሁሉ ጮህንባትና አስቀበልንባት። ‘አህያ ሰጥቶ ሌላ ነገር አምጪ የለም እንዴ?!’ አልኩ.....ገበያተኛው አፌን ይወደዋል። ያልኩት ተተረጎመለት....ሳቀ። የሚያምር ጥርስ ነበረው። ኧረ እሱ እቴ በየቀኑ የማያስተጉዋጉል ጊዮርጊስ የሚሳለም ክርስቲያን ነው በሁዋላ ስንሰማ። ብረት ሁሉ ተባህር ማዶ ያመጣል እና ውሎው ተመኳንንት ነው። በመንገድ ተተገጣጠምን ከበቅሎው ወርዶ ተግቢያችን ድረስ ይሸኘናል። ታዲያ ምን ያደርጋል? ‘ቤት ግባ’ ይባላል። እሷ መቼም አፏ ዝግ ነው፣ አንድ ቀን ‘ግባ’ አልኩት። ከዛ ለመደ። ስንላመድ በተንተባተበ አማርኛ ‘እህ’ አለ። ‘እንዴት እህ?’ ‘ሰብለን ወድጄአታለሁና ዳሩኝ’ ብሎ ፈረንጁ ሽማግሌ ላከ። አንድ ቀን አስቀምጥኩትና ‘ስሚ ሰብልዬ በዛብህ እዝጌር ጋ ነው። አንቺ ዘመድ የለሽ ምን የለሽ። ይሄን ሰው አንድ በዪው። ‘እሺ’ ወይም ‘እምቢ’ አንድ ነገር። ጡር ይሆናል። በዛብህ ጎጃሜው ሞቶ ስደተኛው አርመን ምን በወጣው ይሰቃይ እቴ። ሰብለ ስታገነግን እንደው ያ ደብተራ በድግምቱ አበለሻሽቶአት እንደሁ እያልኩ እቀልዳለሁ። ጎጃሜን በዚህ ጠርጥር።

“ጠዋት እንዲያ አላልኩዋትም? ማታ ላይ: ‘እናንዬ ነጣብኝ’ አትለኝ.... ‘እንዴ እኔ የዘውዲቱ አሽከር፣ ይህቺ ጅል ጎጃሜ ምን ቢያደርጉዋት ይሻላል። ነጣብኝ ብሎ ነገር። እንደው አንቺን ሁለት ቀን ሸክምሽን ትተሽ ባጣጥብሽ ተእሱም አትፈግጊ? ዋናው ልብሽ መከጀሉ ነው’

“አያትህ ሳርኪስ ምን ይመስላል መሰለህ? ረዥም፣ ፊቱ መጠጥ ያለ፣ አገጫም---አገጫምነቱ እንኳን ተእኔ አይብስም፣ ጠጉሩ የሚልፈሰፈስ ጥቁር ነው....በነፋስ እንደተልቆሰቆሰ። ሲመጣ ‘ቡና አፍሉልኝ’ ብሎ እዛ ኮባው ስር ይቀመጣል። ነፋስ አለና እየተመሳቀለ ያስቸግረዋል ጠጉሩ። ‘ምነው እንደ ሴት ጠጉሩ ለስልሶ ምናለ ለእኔ በሰጠኝ’ ስል ሰምቶ ሳቀ....ይሄ ድንጋይ ቤት አልነበረም.....ጣሊያን ገብቶ መች ሰራው.....

“ልጅ አላዛር....ሰማኸኝ?...... ‘አለመታደል’ ትርጉሙ የትም መቸም ያው ‘አለመታደል’ ነው። ብዙ ሳይቆይ ገና ልድራት ዳር ዳር ስል ጣሊያን መጣ። እስኪ ሁሉን እንየውና ሰላም ሲሆን እናስብበታለን ብለን ቆየን። ብዙ ሳይቆይ ‘ማይጨው ላይ ተሸነፍን’ ተብሎ ተወራ ባገሩ። ሬዲዮ የለ ጋዜጣየለ ብቻ ወሬ። ታመስን ታመስን። ሳርኪስና አንድ ባልንጀራው ቤታችን መጥተው ‘ሁሉን ነገር አዘጋጅተናል ወደ ታች ወደ አዋሽ እንሽሽ’ አሉ። ዘመዳችን አይደሉ----ብናውቃቸው። ስንናገነግን ሳርኪስ እንደው ሰብለ እግር ስር በርከክ ብሎ ‘በይ እንሂድ እሺ በይኝ....ብትሞችብኝ ምን ልሆን ነው’ አለ። ብዙ ሳንቆይ ንጉሱ ተሸንፈው ገቡ አዲስአባ። አላመንኩም። ጎበና ቢኖር እላለሁ። ጎበና ቢኖር ሮማ ይገባ ነበር.... አዲስ አይደለም መንከራተት ለእኔ.... መቼም። አይ ጣሊያኑ ይገለናል ወይ ያግዘናል እያልን እንጠብቃለን። ሰው ፈርቶ ወደ ታች ወደ ሲዳሞ ይጎርፋል ነፍሴ ላድን ብሎ። አንድ ቀን ያ ሳርኪስ ከቸች አይል.... በቅሎውን ጭኖ..... ‘በሉ ልወስዳችሁ’....

‘ለመሆኑ የት ልትወስደን ነው?’ አልኩት። ‘ሐረር ወይ ድሬዳዋ ዘመዶች አሉኝ እዛ። ከዛ እናስብበታለን....’ እኔ በተፈሪ ሐረርን አልወደውም። ተፈሪ ሲመጣ ነገር መጣ። ሁሉ ተንኮለኛ ሆነ። እጁን አጣምሮ የፈረንጅ ካቲካላ ለመደና አገሩን ረሳ። ይሄው አስወረረን። ፈረንጆቹ ሲያቆላብጡት ጊዜ ያ ቀጫጫ የተከበረ መስሎታል። ቀን ጠብቀው ልክ አበጁለት....ለኛ ተረፈ እንጂ። ሊለማመጣቸው ተሰደደ አሉ። እሱ ወገኖቹ ላይ ነው ጠመንጃውን አጉርሶ የሚጠብቀው። ወንድ ወንዶቹን እየመረጠ ካ ካ ካ አደረገ። በቃው። ምን ይደረግ ታዲያ....

‘ጣሊያን ተገባ ሰውን አይምረውም’ አለን ሳርኪን። ‘ሴትም አይምርም’ አለን። አይ እዚችው ሞቼ እቀራለሁ የትም አልሄድም። .... ግን የእኔ ሃሳብ የእኔ ነው። አይደለ። አዎ የእኔ የእኔ ነው። ሰብለን እረሳሁዋት። ሳርኪስ የተግደረደርንም መሰለው። ‘እሺ ሰብለ እንኳን ትዳን’ አለ አፍ አውጥቶ፤ መች ገብቶኝ። አይ አሁን በዓይኔ መጣህ አልኳ። አይ የሌላም ነፍስ አላበላሽ ብዬ በመጨረሻ ተረታሁ። እኔ ነበርኩ እምቢተኛዋ። እንግዲህ ተሸሽን ላይቀር በሞጆ እንሂድ ብለን ለስንቅም ለምንም እንዲያመች ተያይዘን እዛ። ሞጆ ትንሽ እንደከረምን ጣሊያን አዲስአባ ገባ የሚል ወሬ መጣ። ያለቀስኩት ለቅሶ። ለሰው እንደማለቅስ። ጎበና እንዲያ ለፍቶ ለፍቶ እንዲያ በባዶ እግሩ ለፍቶ እንዲያ ሆኖ እንዲህ ይሁን?

“አያትህ ሰብለ ነጋ ጠባ ‘ዲማ ምን ሆኖ ይሆን?’ ትለኛለች። ዲማማ ምን ይሆናል ቀጭኑ በላይ መጦለት። ምንም አይሆን። አርመኑ ሞጆ ከረመና ጅቡቲ የሚባለው አገር.... የት አቃለሁ እቴ እንሂድ በሉ ተነሱ ይላል። አይ በቃን አልኩ እኔ። ብንሮጠው የት እንደርሳለን። አገር ሲወሰድ ምን ይደረጋል? ጡብ ሲል ተጉያ፣ ዞር ብሎ ይለቀማል እንጂ። ሰተት ብሎ አይኬድም። አገር ሲወሰድ ደንቡ ‘አምጣው መልስ’ ይባላል። በነገር ሲባል በነገር፣ በጦር ሲሉ በጦር ነው። ተአምላክ ቀጥሎ አገር እኮ ነው። ንክች አልኩ.... ይግረምሽ ሲለኝ ሰብለ ‘እሄዳለሁ’ አለች። ‘ምን?’ ‘እሄዳለሁ’ ‘ምነው ልጄ አሳፈርሽኝ?’ ለሁለታችንም ነዋ የምከራከረው። ደሞ ተባዕድ ጋር ሄዳ ድምፅዋ ቢጠፋ እጠየቅበታለሁ በምድርም በሰማይ። ‘ምን በወጣሽ?’ ‘አብሬው ልሂድ።’ እኔም ነገረኛ ነኝ ብሽቅ ስታደረገኝ ‘ምነው ሰብለ በዛብህን ረሳሽው?’ አልኳት። ካወቅሁዋት ጀምሮ እስክትሞት ድረስ ይህቺን ክፉ ቃል ብቻ ተናግሬአታለሁ። ጊዮርጊስ ምስክሬ ነው.... አንጀቴ ተንሰፈሰፈ። አስለቀስኳት። ዛሬ ሁልጊዜ የምመኘው ነገር ያ ቃል ተአፌ ባይወጣ። የተተፋ አይመለስ። እኔ መች አወቅሁ..... ለካ ከሳርኪስ ጋር እዛው ሞጆ፣ እዛው አፍንጫዬ ስር ነገር ጀምረዋል።

“ሞጆ እንደዛሬ ሳይሆን ሰማይና ደን ነበር። ዛሬ ገደል ብቻ ነው። ልባችን ገደል ሆኖ። ልቡ የለመለመ ሰው ለምለም ይወጣለታል። ገደለ- -ልብ አገርን በገደል ይሞላል። ልቡ የደረቀ አገር ላይ ግራሩ ይደርቃል። ቅንነት ካለህ ደረቅ እንጨት መሬት ብትከት ውሃ ባታጠጣውም ይፀድቃል....

“.....ሰብለን ትቼ የት ልሂድ? በሁዋላ ብጠየቅ ምን እመልሳለሁ። ተነስተን ወደ ሐረር። ብዙ ቀን ተጉዘን ድሬዳዋ ገባን። እዛ ድሬዳዋ ልንደርስ ስንል ሳርኪስን ወባ ጣለችው። የእኔ ወንድም....ጠናችበት..... ብንጸልይ ብናማትብ እሱ ያለው አይቀር ሰብለ ክንድ ላይ ዛ ብሎ ቀረ። አይ የእኔ ጌታ። ዓይኔ ላይ አለ አሁንም። ሳርኪን ሁሌ ዓይኔ ላይ አለ። በኖርኩበት ዘመን ሰው በፊት ለፊት ክፉ ተናግሮኝ ነጅሶኝ አያውቅም። ግን እንዲህ እንዲህ ያለ ነገር ይደርስብኛል። ለምን? በአገር ስለመጣ። በእኔ ሳይሆን በአገር ስለመጣ። ሰብለ የስድስት ወር እርጉዝ ሆና ሞጆ ተመለስን። ሰው ‘ምነው?’ አለ። ‘ሞተ’ ለቅሶ ተቀመጥን። ሰብለ ይህቺን ሲቢርቶ መሰለች። አመዲትን። ለምን አትሁን....

ሲያሽበለብላት ሲያስብላት ነበር። እናትህን ወለደች። አራስ በችግር ከወለደች ሕፃኑ ይደክማል። ክስት ብላ ነበር እናትህ ስትወልድ። ‘ስምዋ ማን ይሁን?’ ሲባል ሰብለ ‘ሮዛ’ አለች። ‘ምንድን ነው ይሄ ደሞ፣ ከየት መጣ?’ ስል። ለካስ ሳርኪስ አድርጊ ብሏት ነው። ‘ወንድ ቢሆንስ ኖሮ?’ ‘ወንድ ተሆነ ‘አላዛር’ በይው’ አያትህ ነው ሊሞት ሲል ስም ያወጣልህ። ታሪክ ነው አይደል። ‘ምን ማለት ነው?’ ስል፣

‘ትርጉሙ ጥጌረዳ ማለት ነው’ አሉ። እሱ ልክ፣ ብትከሳም ጥጌረዳ ትመስል ነበረ። አሁንስ ልጄ ጥጌረዳ አይደለች። ሳንክ የሌላት፣ የእናቷ ልጅ።

“ያን ሰሞን ሞጆ የሚያስገርም ነገር ሆነ። ነሐሴ መሃል ፍልሰታ ማለቂያ ላይ ሌሊት ከሰማይ ወለላ ዘነበ። ልጆች ናቸው እየተጯጯሁ። መጥተው ‘ኧረ ማር ከሰማይ ዘነበ’ እያሉ። ካደርንበት ቤት ስብሳብ ውሃ ያጠራቀመ ቀራፋ ነበር፣ እዛ ያቋረውን ዝናብ ጣቴን ነክሬ ቀመስኩት። ስኳር ስኳር ይላል። አላመንኩም። ያካፋል ገና .... አላቆመም። ወጣ ብዬ እጄን ዘርግቼ ዝናቡን አስነክቼ መዳፌን ስልሰው ስኳር። ሳርኪስ አቅምሶን ስኳር አቃለሁ። ልጆች አፈር በልተው ሊሞቱ፣ ቦይ ውስጥ ያቋረ ውሃ አልቀረም። ተጠጣ። ኡሪው ሁሉ ሰከረ አልኩህ። ዝናቡ አቁሞም ለሁለት ቀናት አፈር እየጠባና ሳር እየጋጠ በስርአት የሚተኛ ልጅ ጠፋ። እኔ የእናትህ ስም ‘ማሬ’ ወይም ‘ስኳሬ’

ቢባል እወድ ነበር። ሳርኪስ በዘሩ ታሪክ አስቀምጦ ሄደ፣ ሞጆስ በልጄ ታሪክ አይኖራትም? ዘመኑስ? በዛ ሰሞን የተወለዱ ሞጄዎች ስማቸው ‘ማር’ ‘ማርዬ’ ‘ስኳር’ ‘ሽኳር’ ‘ወለላ’ ‘ወለላዬ’ ነው የሚባሉት። ሳርኪስ ሰብለን ብቻ ሳይሆነ አንደበታችንንም ነው የወሰደብን። ያን የሰማይ መረቅ የቀመሱ ወንዶቹ ሴቶቹ ብዙዎቹ ዛሬ በህይወት የሉም። ያን ቀምሰው አርበኛ ያልሆኑ ጥቂት ናቸው። ዘፈን ሰምተህ ተሆነ አካም ነጉማ ፈዩማ አካም ነጉማ ፈዩማ ያ ዳሜ ያ ዳሜ ያ ዳሜ ቡልቡላ የሚል ያኔ ነው የተዘፈነው። ቡልቡላ የተባለች ከተማ ስሟ ያኔ ነው የወጣላት አሉ። ምን ታሪክ ታውቅና....ፈረንጅ ሆነህ።

“ነፃነት ተመለሰ። ያም ወሬኛ ንጉስ ነኝ ብሎ። እንግሊዝ እየነዳ አመጣው። ገረሱን አያረጉትም ነበር? በላይን አያረጉትም ነበር? አበበ አረጋይስ? ዞሮ ዞሮ ማን? እሱ። እድሮው መሬቴና ቤቴ ተመለስን። ጎጆዬ ፈርሳ የጣሊያን መኮንን ይሄን ሕንፃ ሰርቶበት አገኘሁ። ቤቱ ይበርደኛል ይሸተኛል....አየር አያስገባ። ይኼው አድሬበት አላውቅም። ከጀርባ ያለው ጭቃ ቤት ነው የምተኛው። ሽሮሜዳ የሚባለው ብዙው ከንግሥት ዘውዲቱ የተሰጠኝ መሬት ነበር። ሸጥኩት። እሱን እየሸጥኩ ቤት ገዛሁ። ቤት እየሰራሁ ማከራየት ጀመርኩ። አይቸግረንም። ሮዛን ደሞ ሰው እየሰደበ አስቸገረን። ‘ክልስ አህያ መልስ’ እያለ። ክፋት ሳይሆን ተጣሊያን የተደቀለች እየመሰላቸው። እንደ አሁኑ ተፈረንጅ መደቀል አይወደድም። ገና ብዙ ነገር አልተረሳማ። አንዳንዴ ሲያስለቅሷት ሽመሌን ይዤ እወጣና ያንን ኡሪ መቀጥቀጥ....አባቷ አርመን ነው እያልን ሰዉ ታገሰ። ዕድሜዋ ደሞ ጨመር ሲል ወንድ አለ እሷ አላይ አለ። ረጋ በሉ እንዴ!!! እሷ ብቻ ሴት ተፈጠረች አሏችሁ እንዴ?!! ትናንት ስድብ ዛሬ ደሞ አይን ማፍጠጥ ምን የሚሉት ዘዬ ነው!....ሰብለ ከሳርኪስ በሁዋላ ማግባት አልፈለገችም። ሁሉ ነገር ልቧን ደፈነው መሰል። የበዛብህ ነገር የሳርኪን ነገር የወላጆቿ ነገር.... ጣሊያን የአንገላታን ነገር....ብቻ ሁሉ ነገር ተጫጭኖአት በሁዋላ ሃብት ብናገኝም ልቧን አልመለሰውም። ውስጥዋ እህህእህህ ነው መቼም። ደሞ....ዝምተኛ ሆነች። ሚስጥረኛም። ልትደብቀኝ አይደለም። ‘ብናገረው ምን ይረባል’ ብላ ነው እሱስ። እህህእህህ ነው ነጋ ጠባ። ‘ማርከሻ ልዳርሽ’ ብላት እምቢ። እምቢ አለች። ደጅ ያልጠና አለ እንዴ? ለነጋድራስ ተሰማ ልጅ ልድራት ሁሉ፣ ማነው ይድነቃቸው ለሚባለው.....ያለ ወተት አትጠጣም። ውሃ አትነካ ምን። ያቺን በቅባ ኑግ የተሰራ ዱባ ወጥ በነጭ እንጀራ ትበላለች እህህእህህ። እህህ እያለች ከወጡ የሚቀረውን ሰሃን ላይ ያለውን መረቅ በጣትዋ ስትዘነቁል፣ በእሱ ስትጫወት ትውላለች። እኛ አገር ከአመት አመት ጦርነት ነበር ልጄ። ስንቷ በሙሽርነቷ ቆማ ቀርታለች፣ እኔም አንዷ አይደለሁ። ስንቷ ባሏን ስንቷ የከንፈር ወዳጇን አጥታለች። ቤት ይቁጠረው። ስንቱ ሎጋ አካለ ስንኩል ሆነ? ባሌ የነበረው የአሰፋ አባት ሱባ ተጠናሁ በሁዋላ አግብቼው..... ማግባት ነው እንዴ? የእኛው አላንስ ብሎ በሌላ ሰው ነገር ገብተን፣ ኮርያ ሄዶ ታሞ መጣ። ብዙ አልቆየም ሞተ....

“እናልህ....ለሌላ ቆስሎ መሞት ምን የሚሉት ዘዬ ነው? እኔ አሁን ‘ኮርያ’ የሚባል አገር ይኑር አይኑር የት አውቃለሁ። ለራሳችን አንሶ ለሰው ተርፈን። ወንድ በዝቶብን ነው እንደ ቡና ወደ ውጭ እንልክ የነበረው? ትሰማኛለህ? ኮርያ ለእኔ ምኔ ነው? ስንቱ ገበሬ በጥልያን ቡዋንብ ተመታ። ዓይኑ ታወረ? ስንቱ ነው ‘መሶሎኒ’ የሚባል ፈረንጅ የሚያውቅ? እንደው በመንገድ ተላልፈው ‘ኖር’ ‘ኖር’ ‘ወያ’ ‘ወያ’ ተባብለው ያውቃሉ? ተዚያ በሶማል በኩል ተዚያ በሐማሴን በኩል በየቦታው ጦርነት። ማን አዘዘ ይሄን ሁሉ? አሁን ደግሞ....በየትምህርት ቤቱ ተማሪ ይራበሻል። እኔ ይኼን አልወድም። ባለፈው እዚህ የተወረወረ ድንጋይ አንድ የቦሊስ ዓይን አጠፋ። አንድ ዓይኑ ፈረጠ። እንዲህ እኛ ሰፈር ተንጋሎ ደሙ ፈሶ ሲያጓራ ነው ያየሁት። የተመታበት ድንጋይ ልጅ የወረወረው አይመስል። ተመሃል ሆሆሆ እያለን የስንት ሰው ቤት ይፈርሳል? እስቲ ንገረኝ። ፊታውራሪ መሸሻ ሰብለን አባረሩ። ጣሊያን እኔን ሰብለንና ሳርኪስን አባረረ። ሳርኪስ ሞተ። በዛብህ ሞተ። በመሸሻና በሞሶሎኒ መሃል ልዩነቱ ምንድነው? በኮርያና በተማሪ ድንጋይ መሃልስ? የእውን ላስብ ብትለው አያሳስብም?

“በዚህ በዚህ በመሳሰለው ተዳከመችና የእኔ እመቤት ታመመች። በሽታዋ ምን እንደሆነ ሃኪም አያውቅ። አልጋ ላይ ብዙ አልቆየችም ያውም። ሞተችብኝ.... ለእኔ ቀረችብኝ እንጂ እሷማ በእግዜር ጋር ናት። እንደተወለደች ነው የተመለሰችው ወደ እሱ ወደ ፈጣሪ። ወደደች አዘነች። ወደደች ወለደች። ጎጃሜም ሆነ አርመን። እግዜር ምን ምን ያህል ወደ ፊት እንደምናዝን ያውቃል። እና የዕንባ መጠን ተመድቦልናል። አንድ ኩባያ የተመደበለት አለ። አንድ ጋን የተመደበለት አለ። የእኔ አንድ እንስራ ሳይሆን አይቀርም። እሱን በአያትህ ጨረስኩ። እሷን አስቤ ከንፈሬን ያልመጠጥኩበት፣ ዘለላ ዕንባ ያልጣልኩበት ጊዜ አለ? እሱው ጊዮርጊስ ያውቃል። ምናል ስትወልድ አንተንም አይታህ ብታልፍ። አየህ አለማለቅ። ተዚህ ነው የጀመርከው። የእግዜርን ሚስጢር ማን ይፈታል? የማን አማርኛ?

“የሱባ ልጅ አሰፋና እናትህ ሮዛ ብቻ ቀሩኝ። ያ ሁሉ ዘመድ አልቆ እነሱ ብቻ። አየህ እሱ ሰው በሞላበት አገር እንዲህ ብቻን ሲያደርግ። ለወሬውማ ሰው ሞቶአል። ለወሬማ ሰው መች ቸገረ.... አሰፋ ለእናትህ ወንድምዋ ነበር። እንደ ዓይኑ ብሌን ነበር እናትህን የሚጠብቃት።

ትሞግድ ነበር። እሱስ እኔም አጥግቢያት ነው። አባትህ ብርሃን የአሰፋ ጓደኛው ነበር። እንደሚወራው ተስተካካይ ተማሪ አልነበረውም። ፈረንጅኛውን ሲነዳው። ግዕዝም ያውቃል አሉ። እስጢፋኖስ ነበር ሰፈሩ። ተዛ እዝህ መስፍን ሐረር ይመጣል። ደጋግሞ ይመጣል። ቆቅ የነበርኩት ሴት ምን እንዳፈዘዘኝ አላውቅም ተሮዛ ለካ ነገር አለው። ለእሷ አይሆንም አፈ ጮሌ ነው። ያው የረባ ጉዋደኛም የላት። ‘ምነ?’ ብትለኝ፣ ቅናታቸው። የእኛ ሰው ቅናት እኮ ደርዝ የለውም....እግዜር በሰራው መልክ ምን ተብሎ ይቀናል?.... አንድ ቀን አፍረቷን ነገረችኝ። ያ ወመኔ አባትህ ብርሃን ለካ አስረግዞአታል። እኔ ሳያት ሮዛ የት ትደርስ አልኩ እንጂ ሌላ ምን አሰብኩ? እሱ ደሞ ይገዝግዘውና እንግሊዝ የሚባለው አገር ለትምህርት ሄዶአል። በደብዳቤ ላይ ደብዳቤ ተፃፈለት። ደብዳቤ በደብዳቤ ላይ። እሱ እቴ ሊመልስ ነው? እንዴ ምን አይነት ነገር ነው? ‘ደስ አለኝም አይባል?’ ጦርን መፍራት ደግ፣ ደሞ ዘርን መፍራት መጣ?

“በክረምት አገሩ ይገባል ተብሎ ቢጠበቅ ቢጠበቅ..... በሁዋላ ስሰማ እሱ በየፈረንጅ አገሩ ‘ፀሐዩ ያምራል’ እያለ ሲዞር ነበር አሉ። ተአመት ተአመት አዲስአባ ጣይ አይደል። ብልግና እንጂ። ንገረኝ እስኪ የተለየ ጣይ ይወጣል? ሁሉ የእግዜር አገር አይደል? አዘንኩ። እሷም ተመሃል አንተን በደህና ተገላገለች። እግዜር ይመስገን። እሷ ዲቃላ ወለድኩ ብላ እንቅልፍ አጥታ።...... ሲመለስ ቢጋቡም እንኳን ሮዛ ቂምዋን አልረሳችም። ትወደዋለች ግን ቂምዋን አልረሳችም። ተሰብለ አባት ተመሸሻ ያልተሻለ ነበር። ‘ብርሃን’ አሉት ስሙን ሲያወጡ። ‘ድቅድቅ ጨለማ’ አይሉትም? አሰፋ አሁን ድረስ አያናግረውም። ብንል ብንል። አሰፋ ሁሉ ነገሩ እንደ አባቱ ፊት ለፊት ነው። አሽሙር አያውቅ፣ ቅኔ አያውቅ። ወዳጅ እኮ ነበሩ..... አባትህን እያማሁት አይደለም፣ ልጄም ነው። እንደ ሮዛ አይነት ሴቶች በብርሃን ማግኘት ይከብዳል። ወዳጆቹ እንዴት እንደሚቀኑበት። እስተዛሬ ያደረጋትን አነሳበታለሁ። ቁም ነገር የመሰለ ነገር ሊያወራ ሲል ‘አይተነው’

እለዋለሁ። ‘አንቺ ደሞ አትረሺም’ ይላል። ‘ወግድልኝ ጃን’......

“......እንደ ብርሃን ዓይነቶች ጠባያቸው እኮ ከንጉሱ ይከፋል። ሰለጠንን ብለው ልባቸው ተደፈነ። ‘እከሌ የሚያምር ማቀዝቀዣ አለው’ ይሉኛል የት ነው የምትሰሩት? ይሄ አቃቂ አገሬ እኮ ነው፣ ‘አቃቂ በረታ’ ስል። ‘አይ ተውጭ ነው የመጣው’ ብለው ይስቃሉ። በራሳቸው ይሳቁ፣ በእኔ ይሳቁ እሱ አልገባኝም። ‘ጀት ያበራሉ’ ይሉኛል። ‘የት?’ ስል ‘ቢሾፍቱ’..... ‘አይ ቢሾፍቱ.....የማትሰራው የለም’ ስል ‘እዛ እኮ ማረፊያዋ ነው የተገዛችውማ ተውጭ ነው’ ይሉኛል። ‘ትልቅዋ እማማ ቀልደኛ ናት፣ የዋህ ናት’ ይላሉ። ‘ኧረ መቀለዴ አይደለም!’ ብል ማን ሰምቶኝ። አትበላውም እንዴ? ሸንኮራህን አንቀርፈህ ታየኛለህ?

ለምን እናና ይሄን ሁሉ እንደምታወራኝ አልገባኝም። ብዙውን ድሮ ሰምቼዋለሁ። እንዲህ ሳስብ:

“ምን ልልህ ነበር? ይሄን ሁሉ ያደነቆርኩህ?” አለች እንደምታስብ ሁሉ አላምጣ የተፋችውን፣ መሬት ያልወደቀ የሸንኮራ ቃጫ ከቀሚሷ ላይ ለማራገፍ እየሞከረች።

“እንደ አያትህ ባትሆን፣ መልኳን አይሁን እንጂ አይንህ ጠቅላላ የእሷ ነው። አይን ብዙ ነገር አለው። እንደ ፅጌ ልበ-ስስ አትሁን። ፅናት አይሆናትም። ታገስኩ ስትል ሆዷን እየበላት አትችልበትም። እራስህን ጥንካሬ አስተምር። የከብት ጥንካሬ ሳይሆን የሰው። የአህያ ሳይሆን የሰው። ፅናትና ስራ አንድ ላይ ጎን ለጎን ካልሆኑ ድንጋይ መሆን ነው። አለዛ ትገፋለህ፣ ገድ ይርቅሃል። ሰማኸኝ?”

“እ”

“እ ትለኛለህ?”

“ምን ልበል እማማ”

“ልክ ነህ ካልደረሰብን አይታወቀንም፣ በል ብላት እሷን እያየሁህ”

በእጄ የያዝኩትን አምሮ የተላጠ ነጭ የሸንኮራ እርሳስ ማኘክ ጀመርኩ።

“ያ ጥግ ይታይሃል? እዚያ ሶስት ጉልቻ ነበር። አንዱ ድንጋይ አሁንም አለ። ሰው ከድንጋይ ያንሳል፣ አንዳንዴ። ያስቀመጡት ቦታ አይገኝም። ሰብልዬ ግን አስቀመጧት የምትገኝ ናት። ከሳርኪስ ወልዳ በዛብህን አልረሳችም። ሳስብ አንዳንዴ ‘አርጅተሽ ነው’ አልባልና እንደው በታምር ከበዛብህ ጋር ዲማ እያለች ሳርኪስን ታልም ነበር? እላለሁ። ሂሂ። እንዴት ሁለት ፍቅር በአንድ ልብ ይቀመጣል። እንዴት አንዱ አንዱን ሳያጣፋ ይሰፍራሉ? እናልህ ያ ድንጋይ አለ። ሁለቱ የት እንደሄዱ እንጃ።”

ጣትዋን ቆጠረችና:

“እስከዛሬ ድረስ አራት ሰራተኛ ነበረኝ፤ አንዷ ጥላው ይሆናል። ከሰብልዬ ጋር ነፋስ እንዳያስቸግረን አሮጌ ጠረጴዛ አጋድመን በእሱ ጋርደን ቡና እናፈላ ነበር። እዛ ጋ እወዲያ ትንሽ መሬት ነበረች....ባዶ ናት እና እሷ ላይ ለክረምት ዘንጋዳ እንተክላለን ለጥንቅሹ ነው ታዲያ። ውልቢኙን በልበላውን በያይነቱ። ክረምቱ ሲያልቅ ቁመቱ ከአጥሩ በላይ ከውጭ ታየዋለህ። ሲደርስልን እሱን መምጠጥ ነው። ማር ማር

ነው የሚል። እጃችን በልጣጩ ሲቀደድ ነበር የሚውል። የመለመልነው ቅጠሉና ልጣጩ ከቦን እንደው ጠረኑ ውል ይለኛል። ዝንጀሮ ያመሰው ይመስላል። ሂሂ.... እራት በልተህ ትሄድ?”

“አይ እላይ ቤት እበላለሁ”

“ጥሩ የዱባ ወጥ አለ”

“አልፈልግም”

“በቅቤ የተሰራ”

“አልፈልግም እማማ አላሰኘኝም”

“የአባትህ ነገር አያስጨንቅህ። ተፈጥሮ ነው። የእውነት። መጥማጥን ዶሮ መሃል ብታደርጋት ያስችላታል? ዶሮንስ ጥሬ በትነህላት ‘አትንኪ’ ብትላት የሚሰማህ አለ?”

“ሂሂ”

“አታስብ፣ አዎ የውሸት ሳቅህ እንጂ እንደ እናትህ አልረሳህም። ነግራኛለች ጠሐይ እንዳዋረዳት። ልኩን እንደመንገር ‘ማርያም ሄደች’ አለችኝ። ማርያም ምን ታድርጋት። የእኔ ሸንኮራ አትለስልስ። ከቻልክ ነው እንግዲህ። ተፈጥሮን ምን ይሰሩታል? .....እንደ እናትህ አትሁን.... ደሞ ዱባ እማትበላው ንቀኸው ነው?”

“ምኑ ይበላል”

“እንዲህ እድሜዬን ያረዘመው ምኑ መሰለህ?”

“ዱባ ስለበላሽ ነው?”

“ወይ ዱባው ነው....ወይ ሸንኮራው ነው....ወይ የመረቀኝ ደግ አለ። እግዜር የእኔን ፀሎት አይሰማም። ያከረመኝ አንተና ጠሐይን በጤና እንዳያችሁ ነው። ሰልዬዋለሁ ብዙ። ተለማምጬዋለሁ። ይኮራብኛል። በሰው ነው የሚሰጠኝ”

“አይ እማማ”

“አሁን ደክሜአለሁ። ይህቺን ደረጃ እንዴት እንደወረድኳት አንተን ላይ። እዚህ ስሆን ነው የምትታየኝ። ተዳገት ተደረጃው ስሆን።” መድረቅ የጀመረው የሸንኮራው መረቅ እጄን ስላጣበቀኝ በጃኬቴ እየጠረኩ ላደርቀው ሞከርኩ።

“እቤት ስትሄድ አታኩርፈው አባትህን። እሷ አሁን ማርያም ጋ ሄዳ ለእሱ ነው የምትፀልየው። ምን ላድርጋት? አሁን ስትሄድ ፊትህን ጎምዘዝ አድርግ። አትደበት፣ ጎምዘዝ በል። ያላማረህ ነገር እንዳለ ንገር። ተረግጠህም አትሳቅ። ጥርሳምና ጅል ነው እንዲያ የሚያደርግ። ጠሐይ ደውላ ትናንት የሆነውን ነግራኝ ማታ አልተኛሁም። መሳቂያ ሆነ.... እሷም መሳቂያ ሆነች። አሁን ማን ተጠቀመ? ወዳጆችህ ሁሉ ነበሩ አሉ”

“ለምን ትደውልልሻለች? እሷ አፏ አያርፍም”

“እንዴ? ልጄ ምን እንደደረሰባት ማወቅ አለብኝ። ደሞ ምን ላደርግስ? ዝም ብዬ ልስማ እንጂ። የማወራው ካንተ ነው። ምነ ተነሳህ?” “ልሄድ። ነገ እመጣለሁ”

“ኧረ አትመላለስ እቴ”

“ግድ የለም። እዚህ ፒያሳ ለሲኒማ ስለምመጣ እግረመንገዴን ብቅ እላለሁ።”

“ነገ ከመጣህ ይሁን አላቆይህ። ሸንኮራዬንም ማምጣት አትርሳ”

“ይሄን መቼ በላሽው። አልጨረስሽውም”

“ያደረ አልበላም።”

ቤት ስገባ፣ የበለጠ መቃቃሩ እንዳይሰፋ ፈርቼ ጥፋቱን አንስቼ አባቴን አልተጋፈጥኩትም። ማግስቱን ብቻ ሳይሆን ለሳምንታት ቤታችን በሚያስፈራ ደርዝ የለሽ ፀጥታ ተወሮ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። የልቡና ነገር ሲጠም ሲጣመም ልክ እንደ ቁስ ሚዛን ያለው አይመስለኝም ነበር። ክብደቱ ዛሬ ድረስ ይሰማኛል።

እናኑን ላያት የተመላለስኩት እስከ የካቲት 1966 አማሃይ አካባቢ ድረስ ነበር። የካቲት 19 የገብሬል እለት ማታ አልጋዋ ላይ ልረፍ ብላ ጋደም እንዳለች ከዚህ አለም ሞት ነጠቃት። እኔና እማማ ተጠርተን ቤቷ ስንሄድ (አባባ ለስራ ጉዳይ ኖርዌይ የተባለ አገር ነበር) አልጋዋ ላይ የምናውቀው ጋቢዋን ከላይዋ ጣል አድርጋ አገኘናት። መሞቷን ስላላመንኩ (ያውም ዘጠና የተጠጋት ሴትዮ) ጋቢዋን ገለል አድርጌ ፊቷን አየሁት። ዐይኖቿ ተከድነዋል። አፏ በትንሹ ተከፍቷል: የመጨረሻዋ እስትንፋስ የወጣችበት ቀዳዳ ይመስላል። የፊትዋ ቆዳ ለስላሳና ቀዝቃዛ ነው። ሽበቷ እንዲህ ነጭ አይመስለኝም ነበር። ከሁለመናዋ የሚወጣው ጠረን የሸንኮራ፣ የዱባና የአሪቲ ነው። ውስጤ ለቅሶ ይሰበስባል፣ አፌ ሊስማት ይቋምጣል። ጉንጭዋ ላይ ጉንጬን አስቀመጥኩ። እንደፈለገችው ባትኖርም ብዙ ያየች ናት። የሚያሳዝን ቢሆንም መታደልም ነው። ጋቢዋን በቀስታ እነበረበት መለስኩት። እማማ ከጀርባዬ ወዲያ ወዲህ እያለች እጆቿን አናቷ ላይ አድርጋ በፀጥታ ታለቅሳለች። ዕንባዋ በጉንጮቿ ላይ መንታ ጅረቶች ሆኖ ይወርዳል። ነጠላዋ በከፊል ገላዋን ለቆ መሬት ላይ ይጎተታል። ቀጭን ቁመናዋ ይንቀጠቀጣል። እንደ ትንሽ ልጅ ነው የምታለቅሰው። ጥቂት ደቂቃዎች በማልቀሷ ብትቀጥል እማዬ ተበታትና ወለል ላይ እንደምትወድቅ እርግጠኛ ነበርኩ። እሷን ደግፌ ለመቀመጥ ተቸገርኩ። ሁለመናዋ ተልቆሰቆሰ። ከተቀመጠችበት ወርዳ እየዳኸች ወደ እማ አልጋ ሄደች። ከዛ ማልቀስ ጀመርኩ። ከአያቴ ሞት የበለጠ የእማማ ሁኔታ ሁሉን ነገር ወደ ቀለጠ የመርዶ አለም ለወጠው። ጥቂት ደቂቃ አልቆየም። እማማ የእናኑን እጅ እንደያዘች ራሷን ሳተች። እናኑ በሞት ከተሰናበተችን ሁለት ሳምንታት ቢያልፈውም እማማ ተዳክማ ከአልጋ አልተነሳችም።

እንደ እናኑ ያሉ እውነቱንና ልዋጩን የማያምታቱ በማጋነንና በማኮሰስ ከትክክለኛ እውነቱ የማያሸሹን ይመጣሉ። የተመደበላቸውን ጊዜ ጨርሰው ወደ ሚሄዱበት ይሄዳሉ። ሁሉ ነገሯ ትዝ ይለኛል። ቀስ ብላ አንስታ አናቴ ላይ የምታስቀምጠው ቆዳው የተጨማደደ የደከመ እጇ፣ በኮረዳነቷ ቅል ስትፍቅ የተጎዱት የመዳፎቿ ጠባሳዎች። በቀስታ የሚፈሰው የሚያስቀኝና የሚያስገርመኝ ጨዋታዋ። ሳይጠፋፉ አብረው የማገኛቸው እውነተኛነቷና ቧልቷ።

አለመስማማትና መስማማት፣ ፍቅርና ፊንታ፣ ጠማማነትና ቀጥተኛነት፣ ገፅና ገበር፣ እናና እንደምትለው እንደ አንጓና መለልታ በቤቴ አህጉር ተቀራርበው የሚኖሩ አልመሰለኝም ነበር። እንዲህ እያየነው አበባ የመሰለው ነገር እሾህ ሆኖ እንደሚወጋን አልገመትንም። ሊታየን የሚገባው ክፉ የማይታየን የዋሃን ነበርን። መልካሙ ያልፋል። ክፉውም ይቀመጣል። ክፉውም ያልፋል፣ መልካሙም ይቀመጣል። የአበባውንና የእሾሁን ወሰን የሚሰብር አደጋ ባልተጠበቀ ቀን እንደሚመጣም ገባኝ። በዚህች አይነት አለም ውስጥ ነበርኩ። ሽሮሜዳ ባሏት መዲባ። እጣ ክፍሌ ካስቀመጠኝ ከዚህች ቦታ የትንሿ አለሜን ወጣ ገባዋ በትንሽ ነፍሴ ሸመደድኩ። ቸኩላ የመጣች የዞረባት ጉርምስናዬን በጠባብ ደረቴ ተቀበልኩ። እየበላሁ፣ እየተፋሁ፣ እያሰብኩ፣ እየረሳሁ፣ ጃርክ፣ ቻቻና ቡጊ ውጊ እየደነስኩ በለግላጋ ቁመናዬ ደቃቃ ዕድሜያትን ሰበሰብኩ....

Tongue, April, 2026. Original Copyright © 2026 by Adam Reta. Published with permission. All rights reserved.